ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ሪፐብሊክ የአየር አገልግሎት ስምምነት አሻሽለው ተፈራረሙ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ እና በፈረንሳይ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል እ.ኤ.አ መስከረም 26 ቀን 2008 ተፈርሞ የነበረው የአየር አገልግሎት ስምምነትን ለማሻሻል ሁለቱ ወገኖች ከመስከረም 26-27/2009 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት ድርድር ተሻሽሎ ተፈርሟል፡፡
 
በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ተወካይ ዋና ዳይሬክተር  አቶ መኮንን ሁነኛው ሲሆኑ የፈረንሳይ ሪፐብሊክን በመወከል ደግሞ የፈረንሳይ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የአየር መንገዶችና የአየር አገልግሎቶች ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት  ሚስተር ሚቼል ላማል  ናቸው፤
 
ስምምነቱ ከ8 ዓመት በፊት በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈረመውን የበረራ ስምምነት አቪዬሽን ከደረሰበት ደረጃና ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ አንጻር በማሻሻል የተፈረመ ሲሆን በስምምነቱም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ
  • የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳመንት ወደ ፓሪስ የሚያደርገውን የመንገደኞች በረራ ከ5 (አምስት)  ወደ 7 (ሰባት) ከፍ እንዲል ተደርጓል፤
  • በአዲስ አበባና በፓሪስ መካከል ወደፊት የጭነት በረራ ለማድረግ ሁኔታዎችን ያመቻቸና 
  • የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈረንሳይ ሃገር ከሚገኙ የባቡር ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ሊሠራ ሚችሉበትን መሠረት የጣለ ነው፡፡
ስምምነቱ በ2ኛው የ5ት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓለማቀፍ መዳረሻዎችን ማስፋትና ማሳደግ በሚል ለተጣለው ግብ ስኬታማነት ግብዓት ከመሆኑም በላይ ከመንገደኛና ጭነት ማጓጓዝ ባሻገር የሁለቱን ሀገራት የንግድ፣የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ፍሰት ለማበረታታትና ለማሳደግ ጉልህ ሚና ያለው ነው፤