ኢትዮጵያና ናይጄርያ የበረራ ስምምነት አሻሻሉ

ኢትዮጵያና ናይጄርያ የበረራ ስምምነት አሻሻሉ ኢትዮጵያና የናይጄሪያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት እ.ኤ.አ በጁላይ 5/2005 ተፈራርመውት በነበረው የአየር አገልግሎት ስምምነት አፈፃፀም ዙሪያ ላይ በመወያየት የመግባብያ ሰነድ ተፈራረሙ።
ሁለቱ ወገኖች እ.ኤ.አ ከታህሳስ 14-15/2016 አዲስ አባባ ላይ ባደረጉት የምክክር ስብሰባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይጄሪያ በሚያደርገው የበረራ አገልግሎት የተጣለውን  ቀረጥ፣ እንዲሁም አየር መንገዱ በናይጄሪያ ከትኬት እና ከልዩ ልዩ አገልግሎቶች ሽያጭ በናይጄሪያ ምንዛሪ (ኒያራ) የሰበሰበው ገቢ በውጭ ምንዛሪ (USD) ለማሰተላለፍ ከናይጄሪያ ባንኮች የገጠመውን ችግር ለመፍታት የናይጄርያ መንግስት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የትራፊክ፣የመንገደኛ እና የካርጎ ምልልስን በተመለከተ በተደረገው ድርድር በሳምንት ቀደም ብሎ ከተፈቀደው 3 የካርጎ ምልልስ በተጨማሪ 9 የካርጎ ምልልስ በመጨመር ወደ 12 የካርጎ ኦፕሬሽን ምልልስ እንዲደረግ ተወስኗል።

የሁለቱ ልኡካን ቡድኖች ከአየር አገልግሎቱ ስምምነት ውጪ በሆኑ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።

ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ተወካይ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ክብረአብ ሲሆኑ የናይጄሪያ ፌዴራል ሪፐብሊክን በመወከል በትራንስፖርት ሚኒስቴር የአየር ትራንስፖርት አሰተዳደር መምሪያ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ራፋኤል አይ ኢዲአሉ ናቸው።