ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሁለገብ ህንፃ ሊገነባ ነው የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ፕሮግራም ተካሄደ፡፡

የዋና መቤት ቢሮ መሠረት ድንጋይ ሲጣልየኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የአገልግሎት አድማሱን መስፋፋት ተከትሎ የተከሰተውን ከፍተኛ የቢሮ መጣበብ ለመቀነስ እና ብሎም የሚሰጠውን አገልግሎት በብቃትና በጥራት ለማከናወን ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ባለስድስት ፎቅ ህንፃ ከ400 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሊገነባ ቅድመ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን በ22/10/2009 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡

የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚንስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ሲሆኑ ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የአለምአቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኦሉሙዪዋ በርናርድ አልዩ፣ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንን ጭምር በዋና ስራ አስፈፃሚ ያገለገሉት ክቡር ዶክተር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡

በእለቱ ንግግር ያደረጉት ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ “ለአቪዬሽን ሴክተሩ የሚደረጉ የአቅም ግንባታ ስራዎች እጅግ ወሳኝ ሚና አላቸው” ሲሉ የገለፁ ሲሆን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የሚገነባው ህንፃም አገልግሎቱን የተቀላጠፈ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል ሲሉ ያላቸውን እምነት ገልፀው ሚንስቴር መስሪያ ቤታቸውም  ጥረቱን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው በበኩላቸው ከ70 ዓመታት በፊት ሶስት ቋሚ ሰራተኞችን ብቻ ይዞ በትንሽ ቢሮ ውስጥ ጎልፍ ክለብ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ስራ የጀመረው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዛሬ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰራተኞችን በመቅጠር የአገልግሎት አድማሱን በማስፋቱ ከፍተኛ የቢሮ እጥረት እየገጠመው ይገኛል፡፡ “በመሆኑም” አሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው “ በመሆኑም ይህ ህንፃ ተገንብቶ  ሲጠናቀቅ አሁን ያለውን የቢሮ ችግር ለመቅረፍ ከመቻሉም በተጨማሪ ለሀገሪቱ ገፅታ ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል” ብለዋል፡፡

የህንፃው ዲዛይን እንደሚያሳየው ህንፃው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ሰራተኞች ዘመናዊና የተመቻቸ  ቢሮ እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በተጨማሪ  የሲቪል አቪዬሽን ሙዝየም፣ የሲቪል አቪየሽን ማሰልጠኛ አካዳሚ፣ የተለያዩ የእስፖርትና የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የመኪና ፓርኪንግና አረንጓዴ እንዲሁም የሚከራዩ ቢሮዎች  የሚኖሩት ሲሆን በቀጣይ በብቃት ማከናወን የሚችሉ  የኮንስትራክሽን ተቋማትን በክፍት ጨረታ በማጫረት የግንባታ ስራው እንደሚከናወን ለመረዳት ተችሏል፡፡