ኢትዮጵያና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአየር አገልግሎት ስምምነት አሻሽለው ተፈራረሙ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ እና በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል ያለው የአየር አገልግሎት ስምምነት ሁለቱ ወገኖች ከመስከረም 3-4/2009 አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት ድርድር ተሻሽሎ ተፈርሟል፤
 
በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮ/ል ወሰንየለህ ሁነኛው ሲሆኑ ዲሞክራቲክ ኮንጎን በመወከል ደግሞ ሚ/ር ኧርነስት ኢላኝዋ ቦናያ (Mr.Ernest ILANG'IKWA BONKANYA) የዲሞክራቲክ ኮንጎ ትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር  የአቪዬሸን አማካሪ ናቸው፤
ስምምነቱ ከ4 ዓመት በፊት የተፈረመውን የበረራ ስምምነት አቪዬሽን ከደረሰበት ደረጃና ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ አንጻር በማሻሻል የተፈረመ ሲሆን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ
  • ለመንገደኛ አገልግሎት ወደ ኪንሻሳ፣ሉሙምባሺና ጎማ ከተሞች በሳምንት 10፣6፣3 የነበረው የበረራ ምልልስ (frequency) ወደ 12፣7፣5 ከፍ እንዲል፤
  • የኪንሻሳ በረራ ከመጪው የፈረንጆቹ የበጋ ወራት (Summer) 2017 ጀምሮ በሳምንት ከ12 ወደ 14 ከፍ እንዲል፤
  • ለጭነት በረራ ለሦስቱም መዳረሻዎች በሳምንት 7 የነበረው የበረራ ምልልስ (frequency) ለያንዳንዱ መዳረሻ በሳምንት 7 ሆኖ በድምሩ ወደ 21 ከፍ እንዲል፣
  • የብሩንዲ መዲና በሆነችው ቡጁምቡራ ላይ ተጥሎ የነበረው የ5ኛ ትራፊክ መብት ክልከላ እንዲነሳ፤
የሚፈቅድ በመሆኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው።
 
ስምምነቱ በ2ኛው የ5ት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓለማቀፍ መዳረሻዎችን ማስፋትና ማሳደግ  በሚል ለተጣለው ግብ ስኬታማነት ግብዓት ከመሆኑም በላይ ከመንገደኛና ጭነት ማጓጓዝ ባሻገር የሁለቱን ሀገራት የንግድ፣የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ፍሰት ለማበረታታትና ለማሳደግ ጉልህ ሚና ያለው ነው፤