የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ትሬይነር ፕላስ (Trainair Plus) ሙሉ አባል ሆነች፡፡

የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ትሬይነር ፕላስ (Trainair Plus) ሙሉ አባል ሆነች፡፡ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ባለሙያዎችን በከፍተኛ ደረጃ ስልጠና መስጠት የሚያስችላት የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ትሬይነር ፕላስ (Trainair Plus) ሙሉ አባል ሆነች፡፡
በአቪዬሽን ዘርፍ ጥቅም ላይ የሚውሉት ቴክኖሎጂዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉና እያደጉ በመምጣታቸው እንዲሁም የአየር ትራፊክ መጠን እየጨመረ በመሄዱ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን በብዛትና በጥራት ማሰልጠን ወሳኝ መሆኑ ይነገራል፡፡
 
በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በቀለ እንዳሉት ማዕከሉ ቀደም ሲል በተለያዩ የአቪዬሽን ሙያዎች ስልጠና ሲሰጥ ቢቆይም አሁን ሙሉ አባልነት ማረጋገጫ የተገኘበት የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ትሬይነር ፕላስ ደረጃ ሃገሪቱ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን እንድትሰጥ፣በዚህም የተሻለ የውጪ ምንዛሪ እንዲገኝ ይረዳል ብለዋል፡፡
 
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ዓለም አቀፉ ድርጅት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ስልጠና ማእከል አሰራርን በመገምገም በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጠው አስተያየትና የግምገማ ውጤት መሰረት እንዲሁም የማዕከሉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ባዘጋጁት ደረጃውን የጠበቀ የስልጠና ሰነድና መርሃ-ግብር /Standardized Training Package/ መሰረት ይህ ደረጃ ሊገኝ ችሏል ብለዋል፡፡
 
ስልጠና ማዕከሉ በአሁን ሰዓት ለ20 ጅቡታያን ሰልጣኞች ስልጠና እየሠጠ የሚገኝ ሲሆን ባለፈው አመትም ለሱማሌ ላንድ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ስልጠና መሥጠቱ ይታወሣል፡፡